ዩኤንዲፒ አህጉራዊ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል በአዲስ አበባ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) አህጉራዊ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል በአዲስ አበባ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከዩኤንዲፒ ፕሮጀክት ጋር አምራች ኢንዱስትሪውን በሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ዙሪያ አብሮ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱም ዩኤንዲፒ ኢትዮጵያ ውስጥ በአምራች ኢንዱስትሪ ዙሪያ ያሉ የፈጠራ ስራዎችን ለመደገፍና አጠቃላይ የአፍሪካን አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታማነትን ለመጨመር የአህጉሩን የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል አዲስ አበባ ላይ ለመገንባት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው መግለጹን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
ዩኤንዲፒ በበርካታ የዓለም ሀገራት ቀጣይነት ያለው ዕድገትን ለማምጣትና ድህነትን ለመቀነስ፣ የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ፣ በፍትህና በመልካም አስተዳደር ዙሪያዎች ድጋፍ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።