አየር መንገዱ ካለው ጥሩ ስም በላይ ከፍ ብሎ እንዲታይ በትጋት እየሰራን ነው – አቶ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ጥሩ ስም በላይ ከፍ እንዲል በትጋት እየተሰራ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡
አቶ መስፍን ጣሰው የአየር መንገዱን የስራ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ የአየር መንገዱ የዘወትር ጥረትና ዓላማ የደንበኞችን አገልግሎት ከፍታ ላይ ማድረስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ደንበኞች በአገልግሎቱ ረክተው ሁል ጊዜም በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲጓዙና ሌሎች አዳዲስ ደንበኞች እንዲመጡ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መለኪያዎችን መሰረት አድርጎ አገልግሎት እያቀረበ እንደሆነ ገልጸው፤ የደንበኞችን አገልግሎት ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል።
ይህም የሆነው ደንበኞች በአገልግሎቱ ረክተው በሰጡት ምስክርነት መሆኑን አንስተው፤ በዚህ ዓመት ብቻ አየር መንገዱ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን መውሰዱን ገልጸዋል።
ለአብነትም ስካይትራክስ የተባለ የእንግሊዝ ሀገር የሽልማት ድርጅት የዘንድሮውን ጨምሮ አየር መንገዱን ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ በማለት ዕውቅና ሰጥቶታል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም አፔክስ የተባለ አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ዓለም አቀፍ የሽልማት ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድን የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ በማለት እውቅና እንደሰጠው ጠቅሰዋል።
አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሰጣቸው የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ጥሩ ስም ያለው መሆኑን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በተሰጡን እውቅናዎች የምንኩራራ አይደለንም ብለዋል።
ጥቃቅን ችግሮችንም ጭምር በማስተካከል አየር መንገዱን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ እንሰራለን ሲሉም አቶ መስፍን በቆይታቸው ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ የአገልግሎት መጓደሎች የሚፈጠሩበት ሁኔታ ይኖራል በማለት ገልጸው፤ ጉድለት ሲያጋጥም በፍጥነት የሚስተካከልበትና የሚሻሻልበት አሰራር መኖሩን ገልጸዋል።
በአመለወርቅ ደምሰው እና ሀይለየሱስ መኮንን