በክልሉ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገልጸዋል።
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛው አመራሮች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙትን የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት÷ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሁሉም ክልሎች ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ክልሉ ባለፉት ዓመታት በነበረበት ውስብስብ የፀጥታ ችግር ምክንያት የልማት ኢኒሼትቮችን ተግባራዊ ለማድረግ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ጠቁመው÷ አሁን ላይ እነዚህን ውስብስብ ችግሮች በማለፍ ወደ ተጨባጭ ለውጥ መሻገር መቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የሚበረታቱ እና በተሰራው ስራ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ ማስቻላቸውንም ጠቅሰዋል።
የተጀመሩ የዜጋ ተኮር የልማት ሥራዎች ለማስቀጠል የተጀመሩ ኢኒሼትቮች ህዝባዊ መሰረት እንዲይዙ መደረጋቸው የሚበረታታ መሆኑን ተናግረው፤ የሌማት ትሩፋት፣ የከተማ ግብርና፣ አረንጓዴ አሻራ እና መሰል ሰው ተኮር ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
የልማት ሥራዎቹ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም ባሻገር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይም ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን አካላት ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ መደረጉ በክልሉ ሰላም ማስፈን እንዳስቻለ ማንሳታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡