አየር መንገዱ የአፍሪካ ኩራት መሆኑን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚጠበቅበት ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሚያከናውናቸውን ተግባራት የበለጠ በማጠናከር የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኩራት የሚለውን ስሙን ማስጠበቅ እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻፀም ገምግሟል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ መሐመድ አብዶ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢትዮጵያ፣ አፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ትልቅ ተቋም መሆኑን አንስተዋል፡፡
አየር መንገዱ ዝናና ክብሩን አስጠብቆ እንዲቀጥል አላሰራ ያሉ አዋጆች ካሉ እንዲሻሻሉ ማቅረብ እንዲሁም የደንበኞች የቅሬታ መነሻ የሆኑ ጥቃቅን ስሞታዎችን አስፈላጊ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ መፍታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴውን ድጋፍ ለሚሹ ጉዳዮችም ድጋፍ እንደሚደረግ ማረጋገጣቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት÷ አውሮፕላንን ጨምሮ በሀብት፣ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ በመጠናከር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እንሠራለን ብለዋል፡፡