በጎንደር ከተማ በ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ነገ ይመረቃሉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው 67 ፕሮጀክቶች ነገ እንደሚመረቁ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ፡፡
ፕሮጀክቶቹ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተቱ የቆዩ መሆናቸውን አቶ ቻላቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ከሚመረቁት ፕሮጀክቶች መካከልም÷ ስምንት ድልድዮች፣ 11 ከትምህርት ቤት ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶች፣ 6 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ እና 21 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን ንጣፍ መንገድ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
ግንባታቸውም በከተማ አሥተዳደሩ እና በግሉ ዘርፍ ድጋፍ መከናወኑን ገልጸው÷ ለከተማው እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ከፀጥታ ጋር በተያያዘ የተሠሩ ተግባራትም ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ይህም በ87 የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች ከ93 ሺህ የሚልቁ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስችሏል ብለዋል፡፡
የሰላምና የፀጥታ ስራውን በዘላቂነት ለማስቀጠልም የማህበረሰብ ዘብ በሚል 1 ሺህ ወጣቶችን በመጀመሪያ ዙር ከተማ አስተዳደሩ እያሰለጠነ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በበረከት ተካልኝ