ሊዮኔል ሜሲ በዓለም አቀፍ ጨዋታዎች የግብ እድሎችን አመቻችቶ የማቀብል ክብረወሰንን ተጋራ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አርጅንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በዓለም አቀፍ ጨዋታዎች 58 የግብ እድሎችን አመቻችቶ የማቀብል ክብረወሰንን ከቀድሞው አሜሪካዊ አጥቂ ላንደን ዶንቫን ጋር ተጋርቷል፡፡
ሜሲ ትላንት ምሽት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አርጀንቲና ፔሩን 1 ለ 0 ባሸነፈችበት ምሽት ለቡድን አጋሩ ላውታሮ ማርቲኔዝ ግብ የሆነችዋን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
ይህን ተከትሎም በዓለም አቀፍ ጨዋታዎች 58 የግብ እድሎችን በመፍጠርና አመቻችቶ የማቀብል ክብረወሰንን ከላንደን ዶንቫን ጋር መጋራት ችሏል፡፡
የቀድሞው የአቬርተንና የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ላንደን ዶንቫን 157 ጨዋታዎችን ለሀገሩ አድርጎ 58 ጊዜ አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን÷ ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ 190 ጊዜ ለአርጀንቲና በመሰለፍ በተመሳሳይ 58 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል፡፡
ብራዚላዊው አጥቂ ኔማር ጁኒየር በ57 የግብ እድሎች ሶስተኛ ደረጃን ሲይዝ÷ ሀንጋሪያዊው አጥቂ ፍሬንክ ፑሽካሽ በ53 እንዲሁም ኬቨን ዲ ቡርይና ከቤልጂዬም ተከታዩን ደረጃ መያዛቸውን ፉትቡም አስነብቧል፡፡