Fana: At a Speed of Life!

የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማዕከላት የማስገባት ሒደት ነገ ይጀመራል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ ተዋጊዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ተሃድሶ ማዕከላት የማስገባት ሥራ በነገው ዕለት እንደሚጀምር የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በሰጡት መግለጫ÷ ተቋሙ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ ማሳካት የሚያስችልና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች መቅረጹን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረትም ከሰባት ክልሎች ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማዕከላት ለማስገባት የመለየት ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

በሁለት ዓመታት ውስጥ በሚከናወነው የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ ከ760 ሚሊየን ዶላር በላይ በጀት መያዙን አንስተዋል፡፡

ከነገ ሕዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮም በመጀመሪያው ምዕራፍ በትግራይ 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በይፋ ይጀመራል ብለዋል፡፡

ለመጀመሪያው ዙር ማስፈጸሚያ ሃብት ከመንግስትና ከለጋሾች መገኘቱን ጠቁመው÷ የተሃድሶ ፕሮግራም ተሳታፊዎች ለ6 ቀናት ወደ ማዕከላት ገብተው የዲጅታል ምዝገባና ማረጋገጥ፣ የሳይኮ-ሶሻልና የሲቪክ ተሃድሶ ስልጠና እንደሚወስዱ ነው ያስረዱት፡፡

የተሃድሶ ፕሮግራም ተሳታፊዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲመለሱ ለመሠረታዊ ፍጆታ እንዳይቸገሩ የመልሶ ማቀላቀል ክፍያ እንደሚሰጣቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.