ጎንደር ከተማን ወደ ታሪካዊ ከፍታዋ የሚመልሱ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው – ም/ ጠ /ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጎንደር ከተማን ወደ ታሪካዊ ከፍታዋ የሚመልሱ የልማት ሥራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በጎንደር ከተማና አካባቢዋ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ የለውጡ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት ለዓመታት ሲጓተት የነበረው በጎንደር አቅራቢያ የሚገኘው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ 24 ሰዓት ያለማቋረጥ በመፋጠን ላይ ነው።
ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረው ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለጎንደር ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
በጎንደር ቆይታችን የታሪካዊው የፋሲል አብያተ መንግሥት ዕድሳት በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑንም ተመልክተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርሱን ታሪካዊ ይዘት በጠበቀ መልኩ ውብ የኪነ ህንፃ ዕድሳት እየተደረገ እንደሆነም አረጋግጠናል ነው ያሉት።
ጎንደርን ወደ ታሪካዊ ከፍታዋ የሚመልሱ የኮሪደር የልማት ሥራዎችም ለከተማዋ ትልቅ የልማት አቅም እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸውየፌደራል መንግሥት በሰጠው ትኩረት ጎንደር ጥንታዊ መንደሮቿ የኪነ ህንፃ ይዞታቸውን ጠብቀው እየታደሱ ነው ብለዋል።
ጎንደር ሰላሟ ተመልሶ የልማት ፕሮጀክቶቿ ቀን ከሌሊት እየተፋጠኑ እንደገና እየታደሰች ወደከፍታዋ እየተመለሰች መሆኑንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ የሚያስፈልገው ሰላምና ልማት መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ሁልጊዜም ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው በጎንደር ብቻ ከ28 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና በዚህም ከ15 ሺ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።