Fana: At a Speed of Life!

የጸረ ተህዋስያን መድሃኒቶችን የተለማመዱ ተህዋስያን እውነታዎች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጸረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች ተህዋስያን መላመድ የበሽታ አምጪ ጀርሞችን ለማስወገድ ጥቅም ላይ የሚውሉ መድሃኒቶች አቅምን ሲፈታተን የሚከሰት ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች በተህዋስያን መለመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሣምንት ተጀምሯል፡፡ በዚህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉዳዩ ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋት የተለያዩ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ባጋራው መረጃ የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶችን የተላመዱ ተህዋስያን ከዓለም አቀፍ የህዝብ ጤና ስጋቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

በዚህም በፈረንጆች 2019 በመላው ዓለም 1 ነጥብ 27 የሚሆኑ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡

በተመሳሳይም መድሀኒት የሚቋቋሙ በሽታ አምጪ ተህዋስያን በተዘዋዋሪ መንገድ ለ4 ነጥብ 95 ሚሊየን ሰዎች ሞት አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሎ ይገመታል።

በሰዎች፣ በእንስሳትና በእጽዋት ላይ መድሃኒቶችን ያለ ሐኪም ፈቃድና ሐኪም ካዘዘው ውጪ መጠቀም መድሀኒት የሚቋቋሙ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እንዲፈጠሩ ዋነኛ መንስኤዎች እንደሆኑ ይነሳል።

መድሀኒት የሚቋቋሙ በሽታ አምጪ ተህዋስያን ቁጥሩ ይነስ ወይም ይብዛ እንጂ በየትኛው የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉ ሀገራትን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡

ሆኖም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ደግሞ የበለጠ ተጎጂ ሲሆኑ ይታያል፡፡ በዚህም ስለመድሀኒት የሚቋቋሙ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚገባ ይመከራል፡፡

ከዚህ በባሰ ደግሞ ብዙ ዋጋ ተከፍሎባቸውና ዓመታትን ወስደው የተገኙ መድሃኒቶችን ዋጋ ቢስ የሚያደርግ ሲሆን፥ በሽታውንም ለማከም አስቸጋሪ ያደርጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እንደአብነት ቀዶ ሕክምና፣ ኬሞቴራፒና ሲ ሴክሽን እንዲሁም ሌሎች የህክምና ሂደቶችን የበለጠ አደጋ ውስጥ የሚጥል እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

በዚህም ዓለም የገጠመውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባ ይመከራል።

መድሃኒት የተላመዱ ተህዋስያን ከሞት እና ከአካል ጉዳት በተጨማሪ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን እንደሚያስከትልም ነው የሚገለጸው፡፡

የዓለም ባንክ በፈረንጆቹ 2050 መድሀኒት የሚቋቋሙ በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን ምክንያት 1 ትሪሊየን ዶላር ተጨማሪ የጤና እንክብካቤ ወጪዎችን እና በ2030 ከ1 ትሪሊየን እስከ 3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር ደግሞ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ኪሳራ እንደሚያስከትል ግምቱን አስቀምጧል።

በሰው ጤና ላይ መድሃኒትን የተላመዱ ተህዋስያን የሚያስከትሉትን ጉዳት ለማስወገድ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ሁሉንም በሽታዎች ከመከላከል መጀመር ይገባልም ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት በመረጃው፡፡

ጥራት ያለው ምርመራ እና ለበሽታው ተገቢ ህክምና ለማግኘት ሁለንተናዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥና ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባም ያሳስባል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.