Fana: At a Speed of Life!

በመርካቶ ህጋዊ ግብይት እንዲደረግ ቁጥጥር እያደረግን ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በመርካቶ ህጋዊ ግብይት እንዲደረግና ለግብይቱ ነጋዴው ደረሰኝ እንዲቆርጥ ቁጥጥር እና ክትትል እያደረግን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አስገነዘቡ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከግብር እና ደረሰኝ መቁረጥ ጋር በተያያዘ ከምክር ቤት አባላት ተቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከንቲባዋ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት÷እንደ ሀገር ያለውን የግብይት ስርዓት በዘላቂነት ለማስተካከል በጥናት ላይ የተመረኮዘ ክትትል ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመርካቶ የገበያ ስፍራ ህጋዊ ግብይት እንዲደረግና ለእያንዳንዱ ግብይት ነጋዴው ደረሰኝ እንዲቆርጥ ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

በተደረገው ክትትል የተገኘው ግኝት በርካታ ህገ ወጥ የሆኑ አሰራሮች እንዳሉ ለመለየት እንደተቻለም አክለዋል፡፡

በዚህም ግማሹ ግብር እየከፈለ ሌላው የማይከፍልበት አሰራር መኖሩን ከነጋዴዎች ጋር ባደረግነው ውይይት እና ክትትል ተገንዝበናልም ነው ያሉት፡፡

ግብር ለማስከፈል እና ደረሰኝ እንዲቆርጡ ለማድረግ በተደረገው ሂደት በሀሰት ውዥንብር በመንዛት መጋዘኖችን በመዝጋት በምሽት እቃዎች ሲጫኑ እንደነበርም መናገራቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህ ፍፁም ስህተት ነው ያሉት ከንቲባዋ በቀጣይ ህጋዊ ስርዓት በመዘርጋት እና ለእያንዳንዱ ግብይት ደረሰኝ እንዲቆርጡ በማድረግ ግብርን በአግባቡ መሰብሰባችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.