Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ÷ በመድረኩ ባለፉት ሦስት ወራት በፓርቲው የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ይገመገማሉ ብለዋል፡፡

በመድረኩ በፓርቲ ደረጃ ላሉ አደረጃጀቶች የተሰጡ ሥልጠናዎች አጠቃላይ ሁኔታ ምን እንደሚመስልም ይዳሰሳል ነው ያሉት፡፡

የፓርቲ መደበኛ ተግባራት አፈፃፀም መመዘኛ ላይም በመወያየት የማዳበር ስራ የመድረኩ አካል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ በተገኙ ተሞክሮዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸው÷ የፓርቲ አባላት ምልመላ፣ ግንባታና ስንብት ረቂቅ መመሪያ እና የፖለቲካ ትንተና ረቂቅ መመሪያ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግ ጠቅሰዋል፡፡

የግምገማ መድረኩ የፓርቲውን አፈፃፀም በጋራ በመገምገም ያለበትን ደረጃ ለመለየትና የቀጣይ የተግባራትን ስኬታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስን ያለመ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በሂደት ጠንካራና ዘመናዊ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በልማት፣ በሰላም፣ ህግና ስርዓትን በማስከበር፣በዴሞክራዊያዊ ስርዓት ግንባታ እና ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትና የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት በሚያስችል መልኩ የትብብር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በግምገማ መድረኩ ላይ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የክልሎችና የከተማ አስተዳደር የፓርቲው ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.