Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ሕዝብ ጎን በመሆን ላሳየችው ቁርጠኝነት ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ ከሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር ተወያይቷል፡፡

የሶማሊላንድ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አሕመድ ሞሃመድ የቀብር ሥነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት በሀርጌሳ ተፈጽሟል፡፡

በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ በአቶ አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት የሥራ ሃላፊዎች ልዑክ ተገኝቷል፡፡

ልዑካኑ በዚህ ወቅት በኢፌዲሪ መንግሰትና ሕዝብ ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸው ÷ ለቤተሰባቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የሶማሊላንድ ሕዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።

በአቶ አደም ፋራህ የተመራው ልዑክ በሀርጌሳ ቆይታው ከሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ በዚህ ወቅት÷ኢትዮጵያ ለጎረቤት ቅድሚያ በመስጠት በአስቸጋሪ ወቅቶች ጭምር ከሶማሊላንድ ሕዝብ ጎን በመሆን ላሳየችው ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።

የቀድሞ ፕሬዚዳንት አሕመድ መሃመድ ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲጠናከር ሃላፊነታቸውን ሲወጡ መኖራቸው ተመልክቷል፡፡

በሕዝቦች መካከል መልካም ጉርብትና እንዲዳብር እና ወንድማማችነት እንዲፀና ላበረከቱት በጎ አስተዋኦም አቶ አደም ፋራህ በኢፌዲሪ መንግስት ስም ያላቸውን ክብር እና ምስጋና ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.