የማህፀን ጫፍ ካንሠር መከላከያ ክትባት መሰጠት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆየው የማህፀን ጫፍ ካንሠር መከላከያ ክትባ ት ዛሬ በተለያዩ ክልሎች መሰጠት ጀምሯል፡፡
ክትባቱ የሚሰጠው ከ9 እስከ 14 ዓመት ለሆናቸው ልጃገረዶች ሲሆን÷ በትምህርት፣ በጤና ተቋማት እና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች በዘመቻ መልክ እየተሰጠ ነው፡፡
በአማራ ክልል በዚህኛው ዙር የክትባት ዘመቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ልጃገረዶች እንደሚከተቡ መገለጹን የባሕርዳር ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ በትምህርት ቤቶች ክትባቱ እየተሰጠ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን ሀቢብ ክትባቱ በ42 ወረዳዎችና ስምንት ከተማ አስተዳድሮች እንደሚሰጥ ጠቁመው÷ በዚህም ከ92 ሺህ በላይ ታዳጊ ሴቶች ክትባቱን እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ክትባቱ የተጀመረ ሲሆን በዚሁ ወቅት የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ መለሰ ኪዊ÷ ለክትባት የደረሱ ሁሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቂ ግንዛቤ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የማህፀን ጫፍ ካንሠር ቅደመ መከላከል ክትባት መሰጠት መጀመሩን የአሥተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ክትባቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በይፋ የተጀመረ ሲሆን፤ መርሃ ግብሩን የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ አስጀምረውታል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተመሳሳይ ክትባቱን በዘመቻ መስጠት የተጀመረ ሲሆን በክትባት ዘመቻውከ157 ሺህ በላይ ሴቶችን ለማስከተብ እቅድ መያዙ ተጠቁሟል፡፡