Fana: At a Speed of Life!

አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ሂደት ኪነ-ጥበብ ትልቁን ሚና ይጫወታል – አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ሂደት ጥበብ ትልቁን ሚና ይጫወታል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ፡፡

‘ባህልና ኪነ ጥበብ ለህዝቦች አብሮነት እና ገፅታ ግንባታ’ በሚል መሪ ሀሳብ ከህዳር 7 እስከ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ለሶስት ወር የሚቆይ ንቅናቄ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተጀምሯል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ አፈ ጉባዔ አገኘው ተሻገር÷ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ዜጎችን ለስራና ለልማት በማነሳሳት የህዝቦችን ሀገር በቀል ልምዶችና እውቀቶችን ለተተኪው ትውልድ በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝኃነትን የተጎናፀፉ ሀገራት የሕዝብ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ ለሀገረ መንግስት፣ ለትዉልድና ማኅበረሰብ ግንባታ ኪነ-ጥበብ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ሂደት ጥበብ ትልቅ አስተዋጽኦ አለዉ ብለዋል::

መንግስት የኪነ-ጥበብ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በማመን የተለያዩ የማበረታቻ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ጥበበኞች ችሎታና አቅማቸውን ተጠቅመው ኢትዮጵያ ያሏትን የጋራ ሀብቶች አጉልተው በማሳየት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው÷ የኪነ ጥበብ በሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ ላይ የልማት ተዋንያን ዜጎችን በማፍራት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ልማትን ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የዚህ መርሐ ግብር ዋና ዓላማም ለዘርፉ ባለውለታዎች ተገቢውን ክብርና እውቅና በመስጠት በትውልድ የሚከበሩበትና የሚታወሱበት እድል መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የዘርፉ ተዋንያን በአወንታዊ የፉክክር መንፈስ ለላቀ ሀገራዊ ስራ እንዲነሳሱ ለማድረግ ነው ብለዋል::

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ራሳቸውንና ሀገርን የሚጠቅሙ የትውልድን ሞራልና ስነ-ምግባር የሚገነቡ የጥበብ ስራዎች እንዲሰሩም ጥሪ አስተላልፈዋል::

በመድረኩ ከተለያዩ ክልሎችና ከሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 67 ባለሙያዎች እውቅና እና ሽልማትእየተሰጠ ይገኛል::

በዘቢብ ተኽላይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.