የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ምደባና ሹመቶች በህገ-ደንቡ መሠረት መከናወናቸውን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ–ምግባር ኮሚሽን የተሰጡ ምደባና ሹመቶች በህገ–ደንቡ መሠረት መከናወናቸውን ገለጸ።
የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ–ምግባር ኮሚሽን ሥራ አስፈጻሚ ያካሄደውን 9ኛ መደበኛ ስብሰባው አስመልክተው የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሠላማዊት ዳዊት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ–ምግባር ኮሚሽን ጠንካራ ኢንስፔክሽን ለጠንካራ ፓርቲ የሚለውን መርህ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ በ2017 በጀት ዓመት “ጠንካራ ኢንስፔክሽን፤ ለጠንካራ ፓርቲ” በሚል በጀመረው ንቅናቄ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
የአሰራር መመሪያዎችን በማዘጋጀት ስራውን በውጤታማነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው÷ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የአፈጻጸም መሻሻል መታየቱን ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በፓርቲ ውስጥ የሚፈጸሙ የምደባና ሹመት እንዲሁም ሌሎች ተግባራት ህገ–ደንቡን መሠረት አድርገው ስለመፈጸማቸው ክትትል ማድረጉን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የፓርቲውን ጤናማነት ማስጠበቅ፣ መገምገም፣ ስልጠናዎችን መስጠት እንዲሁም ግንዛቤ የማስጨበጥ ዓላማ ይዞ ስራዎቹን እያከናወነ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡