የዓለም ጤና ድርጅት የኩፍኝ በሽታ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል አመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት የኩፍኝ በሽታ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ20 በመቶ መጨመሩን አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ በፈረንጆች 2023 ከ10 ሚሊየን በላይ ሰዎች በኩፍኝ መያዛቸውን አስታውሶ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ ከ20 በመቶ በላይ መጨመሩን አስታውቋል፡፡
በሽታው ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ107 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን እና አብዛኞቹ ሕጻናት መሆናቸውን አብራርቷል፡፡
በ57 ሀገራት ላይ በሽታው የጸና እንደነበር በማስታወስ ግማሽ ያህሉ በአፍሪካ መመዝገቡን ነው ያመላከተው፡፡
ተላላፊ ከሆኑ በሽታዎች አንዱ የሆነው ኩፍኝ የጉንፋን ምልክቶች እና ትኩሳት ሊያሳይ የሚችል ሲሆን፥ ይህን እንደተመለከቱ በፍጥነት ወደሕክምና መሄድ እንደሚገባ ይመከራል፡፡
ይህ በሽታ በተለይም በሕጻናት ላይ ከባድ የሆነ ውስብስብ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል መባሉን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡
እየተስፋፋ ያለውን የኩፍኝ በሽታ ለመከላከልም ቢያንስ 95 በመቶ የኩፍኝ ክትባት ሽፋን እንደሚያስፈልግ ዘገባው አመላክቷል፡፡
ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ 83 በመቶ ሕጻናት ለመጀመሪያ ጊዜ ክትባት የወሰዱት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መሆኑን እና 74 በመቶዎቹ ብቻ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ክትባቱን መውሰዳቸው ተገልጿል፡፡
ይህም በአስር ዓመቱ መጨረሻ የኩፍኝ በሽታን የማጥፋት ዓለም አቀፋዊ እቅድን ሊያሰናክል ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረበትም ነው የዓለም ጤና ድርጅት ያመላከተው፡፡