ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከተቋማት ጋር በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ማህበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣት ከተቋማት ጋር በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
ፋና እና ኤፍ ኤች አይ 360(FHI_360 ) የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) በትብብር ያዘጋጁት ከጤና እና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የይዘት ስራዎችን ለማሻሻል የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ማጠናቀቂያ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሥልጠና እና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ከተማ ኃይሉ ÷ ማህበረሰባዊ ለውጥ እዲመጣ ለማስቻል ፋና ከተለያየ ተቋማት ጋር በትብብር መስራቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) አጋር ከሆነው ኤፍ ኤች አይ 360 ፕሮግራሞች ጋር ፋና በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) አጋር የሆነው ኤፍ ኤች አይ 360 ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ ገዛኸኝ በበኩላቸው÷ተቋማቸው ከጤናው ዘርፍ ባሻገር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቀጣይነት ያላቸው ሌሎች ስልጠናዎችን መስጠቱን እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
ፕሮግራሞችን ተደራሽ በማድረግ ረገድም ኤፍ ኤች አይ 360 ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት እና ሰለሞን ይታየው