የጁገል ኮሪደር መልሶ ልማት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጁገል ኮሪደር መልሶ ልማት ስራን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
አቶ ኦርዲን በጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር የመልሶ ልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።
በጁገል ቅርስ የተከናወኑ የኮሪደር የመልሶ ልማት ስራዎችን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፤ የጁገል ቅርስ ህያው ሙዚየም በመሆኑ ቋሚ ጥበቃ እና እንክብካቤ የሚያስፈልገው በመሆኑ ለኮሪደር ልማቱ ልዩ ትኩረት በመስጠት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዓለም አቀፉ የጁገል ቅርስ የማህበረሰቡ ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ መሆኑንም ገልፀዋል።
ካሁን ቀደም በቅርሱ ብሎም በከተማው የተከናወኑ የኮሪደር ልማት፣ የአረንጓዴ ልማት፣ ፅዳትና ውበት ስራዎች አካባቢውን ለነዋሪው ብሎም ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ የቱሪዝም ፍሰቱን ማሳደግ መቻሉንም አስረድተዋል።
በተለይ የኮሪደር ልማት ስራው ዓለም አቀፉን የጁገል ቅርስ ከተደቀነበት ስጋት በማውጣት ህልውናውን አስጠብቆ ማቆየት መቻሉን መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።
በቀጣይም የተስተዋሉ ውስንነቶችን በማረም የኮሪደር ልማቱን በጥራት እና ፍጥነት በማከናወን የቅርስ ጥበቃ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።