Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታጣቂዎች ለክልሉ ሰላም ለመሥራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ለአፋር ክልል መንግሥት አስረክበው ለክልሉ ሰላም እና ልማት በጋራ ለመሥራት ተስማሙ።

የትጥቅ ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ በክልሉ አብአላ ከተማ መካሄዱን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ታጣቂዎቹ የሠላምን መንገድ መምረጣቸው ለክልሉ ብሎም ለሀገራዊ ሠላም እና አንድነት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።

በክልሉ ሠላም እና ልማት ላይ በንቃት መሣተፍ እንዲችሉም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ ስምምነቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦም አመሥግነዋል፡፡

ብርጋዲዬር ጄኔራል ጀማል ሻሌ በበኩላቸው ውይይቶችን በማድረግ ከአፋር ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታጣቂዎች በተጨማሪ ራሱን የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር እያለ ከሚጠራው ታጣቂ ኃይል ጋር በተሠራው ሥራ ወደ ሠላማዊ መንገድ ማምጣት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ በሕገ ወጥ መንገድ ትጥቅ ይዞ የሚንቀሳቀስ የተደራጀ ኃይል አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

ከግጭት እና ጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ የተናገሩት የአፋር ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታጣቂዎች ሊቀ መንበር ስዩም አወል÷ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አክብረን በሠላማዊ መንገድ ሕዝባችንን ለማገልገል በወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.