የቻይና -አፍሪካ የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና- አፍሪካ የኢኮኖሚ እና ንግድ ትብብር ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በኮንፈረንሱ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ እና ሌሎች ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
አቶ አሕመድ ሽዴ÷ የቻይና-አፍሪካ ኮንፈረንስ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን አንስተው የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት እና የጋራ ብልጽግና ለማጠናከር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚ በማስመዝገብ ላይ መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ ÷ለዚህ እድገት ቀጣይነት ገብያ መር የምንዛሬ ፖሊሲ ማሻሻልን ጨምሮ ለቻይና ኢንቨስተሮች ምቹ አሰራር መዘርጋቷን አብራርተዋል::
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው ÷የቻይና እና ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና ንግድ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ በቻይና ዋን ቤልት ፕሮጀክት ሥር ኢትዮጵያ መካተቷ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው አስገንዝበዋል፡፡
የቻይና ትልቅ ግዛት ከሆነችው ጃንግሱ ግዛት የመጡ የልዑካን ቡድን አባላትንም እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸው ቻይና በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰች መሆኑን ገልጸዋል::
የቻይና የንግድ ኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ከአፍሪካ ትልቁ መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡
የጃንግሱ ግዛት ገዥ ዡ ኩንሊን ÷በኢትዮጵያ ለውጥ መገረማቸውን ገልፀው ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ግንኙነት ከኢኮኖሚ በላይ መሆኑን አብራርተዋል።
ጃንግሱ በቻይና ትልቅ የኢኮኖሚ ዞን መሆኗን የጠቆሙት ዡ ኩንሊን ÷ በኢትዮጵያ ከ70 በላይ ኩባንያዎች ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በጸጋዬ ንጉስ