በአፋር ክልል የጤፍ ሰብል የማምረት ባህል እያደገ መምጣቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል የጤፍ ሰብል የማምረት ባህል እያደገ መምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሀመዱ መሀመድ ለፋና ብሮድክሳቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት÷ በአፋር ክልል ያለው የጤፍ ሰብል ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የጤፍ ሰብል ማልማት ተግባርን በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ለማስፋት ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ጀምሩ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
በጥቂት የክልሉ ወረዳዎች የተጀመረው የጤፍ ሰብል ልማት በአሁኑ ወቅት ወደ 28 ወረዳዎች መስፋፋቱን ገልጸው፤ ወረዳዎቹ በኩታ ገጠም ጤፍ ማልማታቸውን ጠቁመዋል።
አሁን ላይም በክልሉ የሚገኙ ከፊል አርብቶ አደሮች፣ ኢንቨስተሮች እና ባለሀብቶች ከዝናብ ባለፈ በመስኖ ጤፍ ማምረት ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በክልሉ የ2016/17 የመኸር ወቅት 8 ሺህ 188 ሄክታር መሬት ላይ የጤፍ ሰብል መልማቱን ተናግረዋል።
የአፋር ክልል በጤፍ ምርት እንደማይታወቅ ገልጸው÷ በክልሉ የጤፍ አምራችነት ባህልን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በሚኪያስ አየለ