የፓኪስታን ባለሀብቶች በአልሙኒየምና በግብርና ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፓኪስታን ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በአልሙኒየም እና በግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።
ባለሃብቶቹ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ ጋር የኢትዮጵያና የፓኪስታንን የንግድ ግንኙነት ለማጎልበት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ወ/ሮ ያስሚን በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ለዓመታት የዘለቀ ጠንካራ የንግድ ግንኙነት ያላቸው ሀገራቱ የሁለትዮሽ ትብብር እና የንግድ ግንኙነታቸው የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ እየተመራ ነው።
የኢትዮጵያን የቅባት እህሎች ገዥ ከሆኑ ሀገራት መካከል ፓኪስታን አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፤ ወደ ፓኪስታን የምንልካቸውን ምርቶች ብዝሀነት በማሳደግ የንግድ ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን በመፍጠሯ የፓኪስታን ባለሀብቶች ያለውን መልካም አማራጮች ሁሉ ተጠቅው በወጪ ንግድ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።
የፓኪስታን ባለሀብቶች በበኩላቸው፤ በአልሙኒየም እና በግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በሀገራቸው ከፍተኛ የጥራጥሬ ምርቶች ፍላጎት መኖሩን በመጥቀስ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች ተጨማሪ ገበያዎችን እንደሚፈጥሩም አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለች በመሆኗ እድገቷን ተከትሎ ለሚፈጠረው የገበያ ፍላጎት ከውጪ የሚገቡትን ምርቶች ሀገር ውስጥ በማምረት እና በወጪ ንግድ ማስፋፋት ሥራዎች በመሰማራት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማገዝ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።