ለአል ሸባብ የሽብር ቡድን መረጃ በማቀበል ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ድሬዳዋ ምድብ 4ኛ ጅግጅጋ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ለአል ሸባብ የሽብር ቡድን መረጃ በማቀበል ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ አምስት ተከሳሾች በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወሰነ።
ተከሳሾቹ ሻለቃ ሀለኔ ኑርዬ ኡመር፣ መሀመድ ጉሀድ አደም እና ኑር ሀሬ ወይም ኑር መህመድ፣ አብዲ አህመድ አብዱላሂ እና ኡመር የሱፍ ሀሰን በኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊትና በሶማሌ ክልል የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪዎች ከክልሉ መርማሪ ፖሊስ ጋር በመሆን ምርመራ ሲያከናውን እንደነበር ይታወሳል።
በፍትህ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ ተረክቦ ተከሳሾቹ መቀመጫውን በሶማሊያ ሀገር ላደረገው ለአል ሸባብ የሽብር ቡድን ድጋፍ ሲያደርጉ መያዛቸውን ጠቅሶ በታህሳስ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በየተሳትፎ ደረጃቸው ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
1ኛ ተከሳሽ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ ክስ ቀርቦበት ነበር።
በዚህም ተከሳሹ የሽብር ቡድኑን ለመርዳት በማሰብ አብዲ ሚሬ ከተባለ የቡድኑ መሪ ጋር በስልክ በመገናኘት የጸጥታ አካላትን በተመለከተ እየተከታተለ መረጃ ሲስጥ የተገኘ በመሆኑ ለሽብር ቡድን ድጋፍ በማድረግ ወንጀል ተከሷል፡፡
በሁለተኛ ክስ ደግሞ 2ኛ ተከሳሽ ላይ በተመሳሳይ ድንጋጌ ስር ክስ የቀረበበት ሲሆን፣ ተከሳሹ በኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ላይ ለመፈጸም ያቀደውን የሽብር ድርጊት ለመርዳት በማሰብ የሽብር ቡድኑ አባል ከሆነው ወላጅ አባቱ ጉሀድ አደን ጋር ስልክ በመደዋወል እና ገንዘብ በመቀበል ስለሶማሊ ክልል ወታደራዊ መረጃ እየተከታተለ ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሲሰጥ የተገኘ መሆኑ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ከ3 እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ ደግሞ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 31/1/ ለ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በዚህም ክስ እንደተመላከተው 3ኛ ተከሳሽ በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም የሽብር ቡድኑ መሪ የሆነው አብዲ ሚሬ የተባለው ግለሰብ በሞባይል ገንዘብ መላኪያ ዘዴ በመጠቀም በተለያየ ጊዜ እና መጠን ለ1ኛ ተከሳሽ የሚላከውን የአሜሪካ ዶላር ወደ ብር መንዝሮ የሰጠ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን 4ኛ ተከሳሽ ደግሞ በዚሁ ፍ/ቤት በሌላ መዝገብ ተከሶ በጅግጅጋ ማረሚያ ቤት ለሚገኘው እና የሽብር ቡድኑ የሀገር ውስጥ ገንዘብ ከፋይ ለነበረው ሱልጣን ሽህ ሀሰን ለተባለው የአል ሸባብ አባል የተለያየ መጠን ያለው ዶላር ተቀብሎና መንዝሮ ሲሰጥ የነበረ መሆኑ ተጠቅሷል።
በ5ኛ ተከሳሽ ላይ በቀረበ ክስ ላይ ተከሳሹ የአል ሸባብ የሽብር ቡድን መሪ የሆነው መሀድ ጆበኔ የተባለው ግለሰብ በሞባይል ገንዘብ መላኪያ ዘዴ በመጠቀም በተለያየ ጊዜ ለ1ኛ ተከሳሽ የሚላከውን ዶላር ወደ ብር መንዝሮ ሲሰጥ የነበረ መሆኑ ተጠቅሶ በአባሪነት በፈጸመው ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀል ተከሷል።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር በችሎት ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊቱን ክደው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ የሰው ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም የቀረበባቸውን ማስረጃ በተገቢው ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
በዚህም የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ አስተያየትን በመያዝ በዛሬው ቀጠሮ 1ኛ ተከሳሽ በ4 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት፣ 2ኛ ተከሳሽ በ5 አመት ፅኑ እስራት፣ 3ኛ ተከሳሽ በ6 አመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።
4ኛ ተከሳሽ በ6 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ4 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲሁም 5ኛ ተከሳሽ በ6 ዓመት ከ6 ወራት ፅኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ