የኢኮኖሚ ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ ጫና እንዳያሳድር የበጀት ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው – ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ላይ ጫና እንዳያሳድር የበጀት ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ፥ እንደ ሀገር የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉ ለኢኮኖሚ እድገት ማነቆ የነበሩ በርካታ ችግሮችን መፍታት አስችሏል ብለዋል።
በዚህም የበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት የተጀመሩ ስራዎች መሬት የሚይዙበት ወሳኝ ወቅቶች መሆናቸውን ጠቁመው አሁን ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪና አጠቃላይ ገበያ እንዳይረጋጋ የሚያደርግ አንድም ምክንያት የለም ብለዋል።
በሩብ ዓመቱ በወጪ ንግድ፣ በገቢና በሐዋላ ፍሰት የታዩ ውጤቶች ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን ፤ከወጪ ንግድ አኳያ በወርቅ የታየው አፈጻጸም ከፍተኛ መሆኑንና በታንታለም የታየው ለውጥም የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ከግብ ለማድረስ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው ያሉት ኢዮብ (ዶ/ር) በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በዲጂታል ዘርፎች የታዩ ውጤቶችም ለውጡ ፍሬ ማፍራት መጀመሩ ለዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
መንግስት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ጫና እንዳያሳድር የበጀት ድጎማ ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩንም አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ባለፉት ወራት የሸቀጦች የዋጋ ሁኔታ እየተረጋጋ መምጣቱንም መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡