ኢትዮጵያና ሩሲያ በካርበን ሽያጭና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በካርበን ሽያጭ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል በሚቻልባቸው ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ከዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደው የሁለቱ ሀገራት ውይይትና ስምምነት ኢትዮጵያ የደን ሽፋኗን ለመመለስና የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመቋቋም የምትሰራውን ስራ ለመደገፍ እንዲሁም በካርበን ሽያጭ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ነው የተፈረመው።
የብሪክስ አባል የሆኑት ሁለቱ ሀገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ ለመቀነስ ኢትዮጵያ እየሰራች ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመደገፍና በካርበን ሽያጭ ላይ በጋራ ለመስራት መፈራረማቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በካርበን ሽያጭና በደን ክብካቤና አጠባበቅ ዙሪያም ቴክኒካዊ ድጋፎችንም ለማድረግ ስምምነቱ እንደሚያግዝ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።