Fana: At a Speed of Life!

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ዴሞክራሲያዊ ልምምድ እንዲዳብር የሚያደርግ ነው – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ እንዲዳብር፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡

“ሀገራዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት መግለጫ÷ በዓሉ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መጥቷል ብለዋል።

በዚህም የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ማስቻሉን ገልጸው፤ በዓሉ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ እንዲዳብር እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ፖለቲካዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በማህበራዊ መስተጋብሩም ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባለፈ አብሮነትን እና ትስስርን የሚያጠናክር ስለመሆኑ አንስተዋል።

ክልሉ ከ32 በላይ ነባር ብሔሮች በ12 ዞን በመፈቃቀድ የመሰረቱትት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የዘንድሮው በዓል በሁለንተናዊ መስክ መነቃቃት የፈጠረ ነው ብለዋል።

በበዓሉ በሚቀርቡ ሁነቶች ክልሉ ያሉትን ዕምቅ አቅሞች የሚያስተዋውቅበት ስኬቱንም የሚያነሳበት እና ልምድ የሚቀስምበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የዘንድሮው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር በአርባምንጭ የሚካሄድ ሲሆን፤ የአርባ ምንጭ ከተማን ጨምሮ የክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የበዓሉ ታዳሚ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸው ተገልጿል።

በወንድሙ አዱኛና ዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.