Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ዲፕሎማሲ ውጤታማ ሥራ አከናውናለች- ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፈው ሩብ ዓመት ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ዲፕሎማሲ ውጤታማ ሥራ ማከናወኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ÷ባለፈው ሩብ ዓመት ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ መካሄዳቸውን በመግለፅ ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ዲፕሎማሲ ውጤታማ ሥራ ማከናወኗን ገልጸዋል።

እነዚህ ኮንፈረንሶች ከገጽታ ግንባታ፣ የቱሪዝም ገቢን ከማሳደግ አኳያ፣ የተለያዩ ልምዶችን በአንድ ቦታ፣ ጊዜ እና ገንዘብ ሳያባክኑ ለማጋራት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው አንስተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) በሩሲያ ሶቺ በተካሄደው የመጀመሪያው የሩሲያ- አፍሪካ አጋርነት ፎረም የሚኒስትሮች ስብሰባ ተሳትፎና የጎንዮሽ የሁለትዮሽ ውይይቶች ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠቡቁ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ በአፍሪካ ቀንድና አካባቢው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ÷ኢትዮጵያ አሸባሪው አልሸባብን በየትኛውም ሁኔታ ለቀጣናው አደጋ ሊሆን የማይችልበት ደረጃ በማድረስ ረገድ የተጫወተችው ሚና በዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ የሚታወቅና ተገቢው ግንዛቤ የተያዘበት መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለብሔራዊ ደኀንነት ሥጋት እንዳይሆንና የተገኙ ድሎች እንዳይቀለበሱ በየትኛውም ሁኔታ አልሸባብን የማዳከም ሥራ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.