በከተማ ልማት ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የከተማ ልማት ዘርፍን በውጤታማነት በመምራት ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
የከተማ ልማት ክላስተር ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።
አቶ አረጋ ከበደ በወቅቱ እንዳሉት÷ የከተማ ዘርፍ ልማት በባህሪው ከፍተኛ ሃብት፣ ቴክኖሎጂና እውቀት ይጠይቃል።
በዚህም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በተጓዳኝ የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በከተማ ልማት ዘርፍ ለማከናወን የታቀዱ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ በየደረጃው ያለውን የሰው ሃይል በማዘጋጀት ማሰማራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ከልል የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የከተማ ዘርፍ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ልማት የሚከናወንበት መሆኑን ገልጸዋል።
በከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡