የእሳት አደጋ መንስዔዎች …
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በየጊዜው የእሳት አደጋ በመኖሪያ እንዲሁም በንግድ ቤቶች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ተከስቶ ጉዳት ሲያደርስ ይስተዋላል፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት እንኳ በአዲስ አበባና አካባቢዉ 127 አደጋዎች ያጋጠሙ ሲሆን ከአጋጠሙት አደጋዎች ውስጥ 63ቱ የእሳት አደጋዎች ናቸው፡፡
በደረሱት አደጋዎች ምክንያትም የ22 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን ጨምሮ 12 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል፤ 93 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡
ታዲያ የእሳት አደጋ በምን ምክንያት ይከሰታል?
የእሳት አደጋ መንስዔዎችን በተመለከተ ሃሳባቸውን ያካፈሉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ የእሳት አደጋ ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች ውስጥ የጥንቃቄ ጉድለት፣ ለአደጋ ከሚያጋልጡ ነገሮች ጋር መለማመድና የአየር ሁኔታ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
አብዛኛው የእሳት አደጋ ከጥንቃቄ ጉድለት የሚከሰት ሲሆን÷ በኤሌክትሪክ ከተገለገልን በኋላ ሶኬት አለመንቀል (አለማቋረጥ)፣ በምንገለገልበት ወቅት መብራት ከጠፋ ሶኬት ሳይነቅሉ ከአካባቢው መራቅ፣ ለጋዝ ሲሊንደር ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረግና ሲገለገሉ የቆዩትን የኤክትሪክ ምድጃ ሳያጠፉ መተኛት ይገኝበታል፡፡
ሌላው ቸልተኝነት ሲሆን ሁኔታው ችግር እንደሚያመጣ እያወቁ ግን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ነገሮች ጋር መለማመድ ለእሳት አደጋ ያጋልጣል፡፡
በተጨማሪም የአየር ሁኔታ ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ ሲሆን ለእሳት አደጋ መከሰትም ሆነ ከተከሰተ በኋላ በፍጥነት ለመዛመት አይነተኛ መንስኤ ነው፡፡
በዚህም ከክረምት ይልቅ በበጋ የእሳት አደጋ የመከሰት እድሉ ሰፊ በመሆኑ ወቅቱን ያማከለ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል አልፎ አልፎ አንዳንድ ሰዎች የእሳት አደጋ ሆነ ተብሎ በሰዎች የሚፈጠር ነው የሚል አስተያት እንደሚነሳ የጠቀሱት አቶ ንጋቱ ማሞ፤ ይህ ፍፁም ከእውነት የራቀ አስተያየት ነው ብለዋል፡፡
አደጋ ሲከሰት እንደ አደጋው ሁኔታ (ክብደትና ቅለት) እና እንደ አቅምና ችሎታችን ቀለል ያለ ከሆነ ሳይዛመት በራስ አቅም ለማጥፋት መሞከር፤ የአካባቢው ሰዎችን አስተባብሮ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በፊት እቃዎችን ማውጣት የአደጋ መጠኑን ይቀንሰዋል ነው ያሉት፡፡
አደጋው የከፋ ከሆነ ግን እራስን እና ቤተሰብን ከአደጋው መጠበቅና ማሸሽ አስፈላጊ ሲሆን፤ ከዚህ ጎን ለጎን ለኮሚሽኑ ሪፖርት ማድረግ ቸል ሊባል አይገባም ብለዋል።
በአጠቃላይ አብዛኞቹ አደጋዎች ከጥንቃቄ ጉድለት የሚከሰቱ መሆኑን ገልጸው፤ የጥንቃቄ መልዕክቶችን መተግበር፣ የአደጋ ቅድመ መከላከል ስራ መስራት፣ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ ገዝቶ ማስቀመጥ፣ ከተቀጣጣይ ነገሮች አካባቢ እሳት እንዳይኖር ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኤሌክትሪክ ከተገለገልን በኋላ ሌክትሪክ ማቋረጥ፣ በምንገለገልበት ወቅት መብራት ከጠፋ ሶኬት መንቀል፣ ለጋዝ ሲሊንደር ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፣ የተገለገሉበትን የኤሌክትሪክ ምድጃ ማጥፋትና ለአደጋ የሚያጋልጡ ልምምዶችን ማስቀረት ይገባል፡፡
በፌቨን ቢሻው