በትግራይ ክልል በመኸር ወቅት ከለማው ሰብል 50 በመቶው ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በ2016/17 የምርት ዘመን በመኸር ወቅት ከለማው 727 ሺህ ሄክታር መሬት ሰብል ግማሽ ያህሉ መሰብሰቡን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ከደነው እንደገለጹት÷ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው።
ግብረ ሃይል በማቋቋም የምርት ብክነትን ለመከላከልና የተገኘውን ምርት በአግባቡ ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ጊዜያዊ አስተዳደሩ 10 ሚሊየን ብር በመመደብ ለአጨዳ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን የማሟላት ስራ ማከናወኑን ጠቁመዋል።
በሰብል ስብሰባው ላይ የፀጥታ ሃይሎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና የትምህርት ማህበረሰቡን ጨምሮ ከ40 ሺህ በላይ የሰው ሀይል እየተሳተፈ መሆኑን አመልክተው፤ በተደረገው ርብርብ እስካሁን 50 በመቶ የሚሆነው ሰብል መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።