ፎረሙ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስተዋወቅ በር መክፈቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ኖርዌይ የቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች፣ የስካንዲኔቪያን ሀገራት ኩባንያዎች እና አልሚዎች በተገኙበት በኖርዌይ ኦስሎ ተካሂዷል።
በኖርዲክ ሀገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር ምኅረተአብ ሙሉጌታ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ መድረኩ ኤክስፖርትን፣ የውጭ ኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም ፍሰትን ለማሳደግ እንዲሁም የተሻለ የፋይናንስ አቅርቦትን ለማመቻቸት ሰፊ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ለማስተካከልም መሰል ፎረሞች አስተዋጽዎአቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው÷ በቀጣይ ኤምባሲው ከመንግስትና ከግል ተቋማት ጋር በቅንጅት መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለውን ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴ ጠቅሰው÷ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ መድረኩ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመሳብ ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡
የኢትዮጵያ በጎ ገፅታ እና የቱሪዝም ሃብት ላይ ገለጻ መደረጉን ያነሱት ደግሞ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ ናቸው።
መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ 24 ፓርኮች እና 18 የኢኮ ቱሪዝም ቦታዎች መከለላቸውን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ሰፊ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት አማራጮች ስለመኖራቸው አስረድተው÷ የዳያስፖራ ማህበረሰቡና ባለሀብቱ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮ-ኖርዌይ ኢንቨስትመንት ግሩፕ መስራችና የቢዝነስ ፎረሙ አዘጋጅ አላሚን ፋሪስ በበኩላቸው÷ መድረኩ በኢትዮጵያና ኖርዌይ መካከል ዘላቂና ቀጣይነት ያለው እድገት ማረጋገጥ እንዲሁም የሁለትዮሽ ግኝኙነትን ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገርን ዓላማ ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብት፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራዎች እንዲሁም የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ ገለፃ መደረጉንም ጠቁመዋል።
በመራኦል ከድር