የሪፎርም ሥራዎች እንዲሳኩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ቦርድ በትጋት እንዲሠራ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተተገበሩ ያሉና በቀጣይ ሊተገበሩ በእቅድ የተያዙ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ቦርድ አባላት ኃላፊነታቸውን እንዲውጡ ተጠየቀ።
ትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ጋር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሪፎርም አተገባበርና ቀጣይ እቅዶች ዙሪያ ምክክር አካሂዷል።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በመድረኩ ላይ÷ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእውቀትና የምርምር ምንጭ እንዲሆኑ የተለያዩ የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የአካባቢያቸውን ጸጋ ተጠቅመው የማህበረሰቡን ህይወት የመቀየርና በሁለንተናዊ ሥራዎቻቸው አርዓያ ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ይህንን ሊመጥን የሚችል የለውጥ ርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
በዚህም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በኃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት ዩኒቨርሲቲዎችን ሊመሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለሚመሩት ዩኒቨርሲቲ ስኬትም ሆነ ውድቀት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው አውቀው ኃላፊነትን መውሰድ እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያስገነዘቡት፡፡