Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ጀማል በከር ላደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረትና አስተዋፅኦ ሽልማት ተበረከተላቸው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በፓኪስታን ላደረጉት መልካም የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዲፕሎማቲክ ኢንሳይት የተባለው ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መፅሄት፤ አምባሳደር ጀማል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሲዮን ከማቋቋም ጀምሮ በሁለትዮሽ፣ በክልላዊ እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን እንዲቀራረቡ መስራታቸውን ገልጿል።

በዚህም ላደረጉት አርአያነት ያለው ጥረት እና አስተዋፅኦ ሽልማቱን እንዳበረከተላቸው አስታውቋል።

በዕውቅና መድረኩ የተገኙት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር አስተባባሪ ራና ኢህሳን አፍዛል ካን አምባሳደር ጀማል ልምድ ያካበቱ ዲፕሎማት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በአውስትራሊያ፣ ባህሬን እና ፓኪስታን ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተልእኮዎችን በከፍኛ ብቃት በመፈፀማቸው እውቅና ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

አምባሳደርር ጀማል ቀደም ሲል ከኢስላም አባድ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የምርጥ አምባሳደር ሽልማት፣ ከፓኪስታን ብሔራዊ የሰላም እና የፍትህ ምክር ቤት የሰላም ሽልማት እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ወንድማማችነትን ለማጠናከር ላደረጉት ጥረት ከኮምስቴክ የአመቱ ምርጥ አምባሳደር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በካራቺ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ እንዲጀምር፣ የንግድ ልዑካን ቡድኖች ወደ ሀገራቱ በመላክ፣ በንግድ፣ በጤና፣ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የመግባቢያ ሰነዶች እንዲፈረም በማድረግ ሰፊ ስራ መስራታቸውን በኢስላም አባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመልክቷል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጀመሩትን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በፓኪስታን እንዲጀመር አምባሳደር ጀማል አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተጠቅሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.