በፍራንኮ ቫሉታ ይገቡ የነበሩ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በመደበኛ የንግድ ባንኮች የመተማመኛ ሰነድ እንዲገቡ ተወስኗል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍራንኮ ቫሉታ ከውጭ የሚገቡ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በመደበኛ የንግድ ባንኮች የመተማመኛ ሰነድ (ኤል ሲ) አማካኝነት እንዲገቡ መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡
መንግስት በመሰረታዊ የንግድ ሸቀጦች ላይ የምርት እጥረት እንዳይከሰት በማሰብ ለግል ባለሀብቶች ፍራንኮ ቫሉታ መፍቀዱንም አስታውሰዋል፡፡
ፍራንኮ ቫሉታ መሰረታዊ ሸቀጦችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የምርት እጥረት እንዳይከሰት የተወሰነ እገዛ ማድረጉንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የፍራንኮ ቫሉታ ባልተገባ መንገድ ለጥቁር ገበያ በመጋለጡ በውጭ ምንዛሬ ላይ ጫና በማሳደር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዝኗል ብለዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራው በመደበኛውና በትይዩ ገበያው መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ተቀራራቢ በማድረጉ የፍራንኮ ቫሉታ እንዲነሳ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በሂደት ላይ ያሉ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች በሁለት ሳምንታት ውስጥ እንዲገቡ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
በውሳኔው መሰረትም ከውጭ የሚመጡ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በንግድ ባንኮች የመተማመኛ ሰነድ ብቻ እንዲገቡ መወሰኑንና ይህም ወደ ተግባር መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡
የንግድ ባንኮች ለመረሰታዊ ሸቀጦች የሚሆን በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዳላቸው ጠቅሰው÷ ባንኮች ለሸቀጦች ትኩረት ሰጥተው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲያሻሽሉ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት የመሰረታዊ ሸቀጦችን አቅርቦትና ዋጋ በማረጋጋት የፖሊሲ ርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያደርግም አመላክተዋል፡፡
መንግስት በወሰዳቸው የቁጥጥርና የፖሊሲ ርምጃዎች በትይዩ ገበያውና በመደበኛ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት መጥበቡንም አስድተዋል፡፡
በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራው የውጭ ምንዛሪ ተመን መዋዠቅ አላጋጠመም ያሉት ሚኒስትሩ÷ በቀጣይም በብሔራዊ ባንክ በኩል የተጠናከረ ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡