በሳንባ ምች በሽታ የሚከሰት የታዳጊ ህፃናት ሞት 67 በመቶ መቀነሱ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳንባ ምች በሽታን የመከላከሉ ተግባራት በበሽታው የሚሞቱ ህፃናትን ቁጥር በ67 በመቶ መቀነስ መቻሉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ15ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ “የሳንባ ምችን ለመግታት ግንባር ቀደም እንሁን” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን አለም አቀፍ የሳንባ ምች ቀን ምክንያት በማድረግ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የክልል ጤና ቢሮዎች የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በዚሁ ወቅት ÷ ሚኒስቴሩ የሳንባ ምችን ጨምሮ ተላላፊ ህመሞችን ለመከላከል የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጨማሪ ስራ የሚጠይቁ እንደሆኑ ገልጸዋል።
በሽታውን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት በበሽታው የሚከሰት የታዳጊ ህፃናትን ሞት 67 በመቶ መቀነስ መቻሉንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡