በቻይና በመኪና አደጋ የ35 ሰዎች ህይዎት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡባዊ ቻይና ዙሃይ ስታዲየም ውስጥ አንድ ግለሰብ በብዙ ሰዎች መሃል መኪናውን ይዞ በመግባቱ ቢያንስ የ35 ሰዎች ህይዎት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
አደጋው ፋን የተባሉ የ62 ዓመት ግለሰብ መኪናቸውን በዙሀይ ስፖርት ማእከል በተከለከለ ስፍራና ያለጥንቃቄ በበርካታ ሰዎች መሃል ሲያሽከረክሩ የደረሰ መሆኑን የገለጹት የአካባቢው ፖሊስ ፥ጥቃቱ ከባድ እና አስከፊ ነው ብለውታል፡፡
በአደጋው የ35 ሰዎች ህይዎት ሲያልፍ ከ43 በላይ ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት አስተናግደዋል የተባለ ሲሆን÷ከቆሰሉት መካከል በርካታ አዛውንቶች፣ ታዳጊዎች እና ህጻናት እንደሚገኙበት የቻይና መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ፖሊስ እንዳስታወቀው ፥ አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ቢውሉም ለማምለጥ ሲሞክሩ በደረሰባቸው ጉዳት በአሁኑ ወቅት ጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ።
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ ÷በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ተገቢው ህክምና እንዲደረግላቸውና ጉዳት ያደረሱት ግለሰብ ላይ ከባድ ቅጣት እንዲጣልባቸው ጠይቀዋል፡፡
በአደጋው መንስኤ ምርመራም ግለሰቡ አደጋውን ያደረሱት በፍቺ ወቅት በነበረ የንብረት ክፍፍል ባለመደሰታቸው ሊሆን እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል።
ግለሰቡ አሁንም ጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ስለሚገኙ እስካሁን ምንም ዓይነት ጥያቄ ሊቀርብላቸው አለመቻሉንም ፖሊስ ተናግሯል።