የሰንዳፋ በኬ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሕንጻ ግንባታ መሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የሰንዳፋ በኬ ከተማ አሥተዳደር የፖሊስ መምሪያ ሕንጻ ግንባታ ማስጀመሪያ መሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።
ኮሚሽነር ጀነራሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የሚገነባው ሕንጻ የከተማውን ሰላምና ደኅንነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለከተማው ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲም አሁን ላለበት ደረጃ መድረሱ የከተማውን ገፅታ እንደሚቀይረው በማንሳት÷ ከአፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት ለጉብኝት ብሎም ለትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደሚመጡ ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ለከተማዋ ፈጣን ዕድገት እና የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ዕድል ይፈጥራል ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ዕድገት ከከተማዋ ዕድገት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ዘመናዊ የደኅንነት ካሜራ የመዘርጋት ሥራ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የፖሊስ ጣቢያ ይገነባል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የኦሮሚያ ፖሊስ አመራሮችና የአካባቢው ማኅበረሰብም ለፕሮጀክቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡