በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ማሣ ወደ ዘመናዊ የመሬት መረጃ ስርዓት ተሸጋገረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ማሣ ወደ ዘመናዊ የመሬት መረጃ ስርዓት መሸጋገሩ ተገለጸ፡፡
በክልሉ ግብርና ቢሮ በካልም ፕሮግራም የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዕቅድ አፈጻጸም እና በቀጣይ ተግባራት ዙሪያ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በዱራሜ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡
በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱል ሀፊዝ ሁሴን በወቅቱ እንዳሉት÷ 1 ሚሊየን 502 ሺህ 877 ማሣ ወደ ዘመናዊ የመሬት መረጃ ስርዓት እንዲሸጋገር ተደርጓል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት 1 ሚሊየን 658 ሺህ 870 ያህል ማሣ የመሬት ልኬት ተካሂዶ ለአርሶ አደሩ የባለቤትነት ደብተር መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ በመሬቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የተጀመሩ ሥራዎችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አቶ አብዱል ሀፊዝ ገልጸው፤አርሶ አደሩ ለፋይናንስ ተቋማት ደብተር አስይዞ የግብርና ግብአት እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ሥራ ማከናወን መቻሉን ጠቁመዋል።
በግብርናው ዘርፍ ጠንካራ ተቋም በመገንባት ሂደት የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅም ሥራ አስኪያጁ መጠቆማቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡