በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ግጭት በማስነሳት የሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ያደረጉ 13 ተከሳሾች በጽኑ እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ነዋሪዎች እርስ በርስ እንዲጋጩ በማድረግ የሰዎች ሕይወት እንዲጠፋና ዜጎች እንዲፈናቀሉ አድርገዋል የተባሉት 13 ተከሳሾች በጽኑ እስራት ተቀጡ።
የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ-መንግስትና ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ በ2013 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) (ለ)አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 240 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም ተከሳሾች ለጊዜው ካልተያዙ ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ከጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዲላ ጎጎላ ቀበሌ 01 የሚባል አካባቢ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ የነበረ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሌላ ስራ አከባቢውን ለቆ ሲወጣ ተከሳሾች ከተሸሸጉበት ስፍራ በመውጣት የተለያዩ ጦር መሳሪያዎችን በመያዝ እየዘፈኑና እየጨፈሩ የአከባቢው ሰዎች እንዲቀላቀሏቸው በመቀስቀስ ሲያስፈራሩ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በወቅቱ በዲላ ጎጎላ 01 ቀበሌ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የነበሩ ሰነዶችና ንብረቶችን ሲያቃጥሉ እንደነበርም በክሱ ተመላክቷል፡፡
በጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ከቀኑ 9 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ የሌሎች ብሔር ተወላጆች የሚኖሩበት ሥፍራ በመሄድ “ለስብሰባ ስለምትፈለጉ የእኛ ወታደሮች ኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መጥተው ያናግሯችኋል” በማለት ነዋሪዎችን ወደ ስብሰባው ቦታ እንዲሄዱ እና አንድ ቦታ እንዲሰበሰቡ በማድረግ የተለያዩ የጦር መሳሪያ ከያዙ የኦነግ ሸኔ አባላት ጋር ዙሪያቸውን ከበው በጭካኔና ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ 36 ሰዎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም 20 የሚሆኑ ዜጎች የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ያደረጉ ሲሆን÷1ሺህ 44 የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው በክሱ ተገልጿል።
በተጨማሪም ለጊዜው ካልተያዙ ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ንብረት በመዝረፍና በማቃጠል አጠቃላይ 10 ሚሊየን 601 ሺህ ብር የሚገመት የንብረት ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ በሕዝቡ ደህንነት እና ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ በማስከተል እና የሰው ሕይወት በማጥፋት፣ አካል ጉዳት በማድረስ እና በማፈናቀል በየተሳትፎ ደጃቸው ተጠቅሶ በፈፀሙት አንዱ ወገን በሌላው ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሳ በማነሳሳት የእርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ ማድረግ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በዚህ መልኩ ተሳትፏቸው ተገልጾ በቀረበባቸው የክስ ዝርዝር ሊይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የሰጡትን የዕምነት ክሕደት ቃላቸውን ተከትሎ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክር ማስረጃ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በየደረጃው እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ሲሆን÷ ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል ባለመቻላቸው ተጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ ተከሳሾች ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝና ሌሎች አጥፊዎችን ሊያስተምር ይችላል ያለውን ታሳቢ በማድረግ በዛሬው ቀጠሮ በ1ኛ፣2ኛ ፣3ኛ፣4ኛ፣6ኛ ፣9ኛና11ኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ14 ዓምት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
32ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ7 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በሌለበት መወሰኑ ነው የተመላከተው፡፡
10ኛ ተከሳሽን በሚመለከት በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ያዘዘው ፍርድ ቤቱ÷በ13ኛ፡14ኛ፣ 16ኛ፣ 17ኛና 18ኛ ተከሳሾች ላይ ደግሞ ከ5 ዓመት እስከ 6 ዓመት ከ6 ወራት በሚደርስ ጽኑ እስራት ከተያዙበት የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የሚታሰብ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ እና ቅጣቱን የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
ያልተያዙ ተከሳሾች በሌሉበት የተቀጡ መሆኑን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ አፈላልጎ ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲያስረክብና የአዲስ አባበ ማረሚያ ቤት ቅጣቱን እንዲያስፈጽም ታዝዟል፡፡
በዚህ መዝገብ ላይ ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ በብይን ነጻ የተባሉ ተከሳሾች እንደነበሩ የሚታወስ ነው።
በታሪክ አዱኛ