ሂዝቦላህ 50 ሮኬቶችን ወደ ሰሜን እስራኤል አስወነጨፈ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ 50 ተጨማሪ ሮኬቶችን ወደ ሰሜን እስራኤል ማስወንጨፉ ተሰምቷል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ ሂዝቦላህ በሰሜን እስራኤል ካርሚኤል በተሰኘ አካባቢ 50 ሮኬቶን አስወንጭፎ በፈጸመው ጥቃት እስካሁን ከ6 በላይ ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከተተኮሱት ሮኬቶች የተወሰኑት በሚሳኤል መቃወሚያ የከሸፉ ሲሆን÷ ሌሎች ደግሞ ኢላማቸውን ሳይመቱ መቅረታቸውን ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡
በአንጻሩ የእስራኤል ጦር በሰሜን ጋዛ እና በሰሜን ሊባኖስ የሚፈጽመው የአየር ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተነግሯል፡፡
ጦሩ በሰሜን ሊባኖስ በፈጸመው ጥቃት 23 ሰዎች ለሕልፈት መዳረጋቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ በሰሜን ጋዛ ጃባሊያ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ 36 ሰዎች መገደላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተለያዩ ሀገራት እስራኤል፣ ሂዝቦላህና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ በማቅረብ ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡