የፀረ-አበረታች ቅመሞች የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ አትሌቶች የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ህብስት ጥላሁን፣ ሳሙኤል አባተ እና ፀሐይ ገመቹ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን (ዶፒንግ) በመጠቀም የሕግ ጥሰት መፈማቸው ተረጋገጠ፡፡
በዚህም መሠረት አትሌት ፀሐይ ገመቹ በተደረገላት የአትሌት ባዮሎጂካል ፓስፖርት (ABP) ምርመራ አበረታች ቅመም መጠቀሟ መረጋገጡን የኢትዮጵያ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በፈረንጆቹ ከጥቅምት 30 ቀን 2024 ጀምሮም ለ4 ዓመታት በማንኛውም የስፖርት ውድድር እንዳትሳተፍ ተወስኗል፡፡
በተጨማሪም ከ2020 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2024 ጀምሮ ያስመዘገበችው ውጤት እንዲሰረዝ ቅጣት ተጥሎባታል።
እንዲሁም አትሌት ህብስት ጥላሁን ቻይና ሀገር ውስጥ በነበረው ውድድር ላይ በተካሄደው ምርመራ Triamcinolone acetonide የተባለውን የተከለከለ ንጥረ ነገር መጠቀሟ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
በዚህም መሠረት በፈረንጆቹ ከሰኔ 3 ቀን 2024 ጀምሮ ለ2 ዓመታት በማንኛውም የስፖርት ውድድር እንዳትሳተፍ እገዳ ተጥሎባታል መባሉን የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አትሌት ሳሙኤል አባተ በፈረንጆቹ የካቲት 29 ቀን 2023 በተካሄደው ምርመራ EPO (Erythropoietin) የተባለውን የተከለከለ ንጥረ ነገር መጠቀሙ ተረጋግጧል ነው የተባለው፡፡
በመሆኑም በፈረንጆቹ ከሚያዝያ 17 ቀን 2024 ጀምሮ ለ2 ዓመታት በማንኛውም የስፖርት ውድድር እንዳይሳተፍ እገዳ ተጥሎበታል፡፡
በቀጣይም በኢትዮጵያ በየደረጃው የሚደረገው ምርመራና ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው፡፡
ባለስልጣኑ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀምም ይሁን በተለያዩ መልኩ የፀረ-ዶፒንግ የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አትሌቶችና ከጀርባ ሆነው በሚተባበሩ ሌሎችም ግለሰቦች ላይ የሚወስደውን የእርምት ርምጃ እንደሚያጠናክርም አመላክቷል፡፡