በመርካቶ የተረጋጋ ግብይት አለ!
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በመርካቶ አካባቢ አንዳንድ ነጋዴዎች “ንብረት ሊወረስ ነው፤ ሱቃችን ሊዘጋ ነው” የሚል ውዥንብር ውስጥ መግባታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተመልክተናል፡፡
ውዥንብሩ ከየት መጣ? የሚለውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው ማጣራት፤ በደረሰኝ እንዲገበያዩ የሚጠበቅባቸው ነጋዴዎች በዚህ ሂደት እንዲያልፉ በሚደረገው ሥራ ሳይሆን እንዳልቀረ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
በመዲናዋ አንዳንድ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን ሥርዓት ለማስያዝ እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በደረሰኝ እንዲገበያዩ የሚጠበቅባቸውን ነጋዴዎች በመለየት በደረሰኝ ግብይት እንዲፈጽሙ በርካታ ውይይቶች ተደርገው መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህን መግባባት ወደ ጎን በመተው እና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት እየተከናወነ ያለውን ሥራ ለማስተጓጎል ያሰቡ አንዳንድ አካላት ንብረት ማሸሽን ጨምሮ ሱቅ ሊዘጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም አንዳንድ አምራች፣ አከፋፋይ እና ቸርቻሪ ነጋዴዎች ያለደረሰኝ መገበያየት በገንዘብ እና በወንጀል እንደሚያስቀጣ ሊገነዘቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ እና በአንዳንድ አካላት “በመርካቶ ነጋዴው ፈርቶ ሱቁን ዘግቷል፤ ያለወትሮ አስፋልቱ የኳስ መጫወቻ ሆኗል” በሚል እየተናፈሰ ያለው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ጠቅሰው÷ “በመርካቶ በአብዛኛው የተረጋጋ ግብይት አለ” ብለዋል፡፡
ምናልባት ግብይት ሲፈጽሙ ደረሰኝ እንዲጠቀሙ የተለዩ ነጋዴዎች ይህን ላለመተግበር ንብረት እያሸሹ እና ሱቆችን እየዘጉ ከሆነ ተገቢ አለመሆኑን አሳስበዋል፡፡
እኛ በመርካቶ እያከናወንን ያለነው ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ነው፤ ለዚህም የንግዱ ማኅበረሰብ ተባባሪ ሊሆን እንጅ ሊያፈገፍግ አይገባም ብለዋል፡፡
አንዳንድ ያለደረሰኝ በመገበያየት ሕዝብና መንግሥት ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እያሳጡ የራሳቸውን ኪስ የሚሞሉ አካላት እንዳሉ ጠቁመዋል።
ምናልባት ካሁን በፊት ያለደረሰኝ የተገዙ ዕቃዎች ካሉም ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የማስመዝገብ ሥራ እንዲያከናውኑ ቢሮው ለነጋዴዎች ማሳወቁንም ነው የተናገሩት፡፡
ብልሹ አሠራርን ጨምሮ ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙ ካሉ ህብረተሰቡ በ7075 የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዮሐንስ ደርበው