ከ294 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከጥቅምት 22 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 294 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መያዙን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 14 ተጠርጣሪ ግለሰቦች እና 7 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡
ከተያዙት ዕቃዎች መካከልም አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ መድኃኒት፣ የምግብ ዘይት፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እና የወጭ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ የገቢ እና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ እና ሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ቀዳሚ መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡