ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለማስፈን ቁርጠኛ ናት- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በሩሲያ-ሶቺ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ተሳትፏል፡፡
ጉባዔው በሩሲያ እና አፍሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነትን ያጎላ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ዓላማን ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ እና ሩሲያ መካከል በተለይም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ዘርፎች ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የጋራ ተጠቃሚነትን ከፍ ለማድረግም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ትብብር ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
ምርታማነትን ማሳደግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያሉትን መጠቀም፣ ኢንዱስትሪን ማስፋት የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን በመፍታት ረገድ ቁልፍ መስኮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጠቃላይ ማሻሻያ ለማድረግ እና አፍሪካ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንድታገኝ ሩሲያ ድጋፍ ለማድረግ ያላትን ዝግጁነት ኢትዮጵያ በደስታ ትቀበለዋለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቁርጠኛ ናት ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ከጉባዔው ጎን ለጎንም ሚኒስትሩ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የውጨ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡