Fana: At a Speed of Life!

ተመድ በሰሜን ጋዛ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ጋዛ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት የዕርዳታ ሥራዎች ኤጀንሲ አስጠንቅቋል፡፡

የኤጀንሲው ኮሚሽነር ጀነራል ፊሊፕ ላዛሪኒ በሰጡት መግለጫ÷ በጋዛ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው፤ ከዚህ በከፋ ሁኔታም በሰሜን ጋዛ ረሃብ ሊከሰት ይችላል ብለዋል፡፡

ወደ ጋዛ እየገባ ያለው ሰብዓዊ ዕርዳታ በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው÷ በአማካኝ በቀን ከ30 በላይ የጭነት መኪኖች ቢገቡም ይህ የፍልስጤም ሕዝብን የዕለት ምግብ ፍላጎት 6 በመቶ ብቻ እንደሚሸፍን አስረድተዋል፡፡

ይህም በጋዛ ውስጥ ያሉትን ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ከበቂ በታች ነው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ወደ ሰሜናዊ ጋዛ የሚገባውን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲጨምር አስቸኳይ ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ያቀረቡት ኮሚሽነር ጀኔራሉ÷ አሁንም ችግሩን ለመቅረፍ ጊዜው አልረፈደም ማለታቸውን ኤሚሬትስ ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (አይ ፒ ሲ) አካል የሆነው የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴም÷ በሰሜን ጋዛ ሊደርስ ስለሚችለው ረሃብ በሰጠው ማስጠንቀቂያ አስከፊ ሁኔታ እንዳይከሰት በቀናት ውስጥ አስቸኳይ ርምጃ ያስፈልጋል ብሏል፡፡

በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ያመላከተው የኮሚቴው ሪፖርት÷ እያንዣበበ ያለውን ረሃብ ለማስወገድ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.