ቤኑና መንደር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ሀገርን በትጋት ለመለወጥ ትምህርት የሚወሰድበት ነው -ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ቤኑና መንደር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ሀገርን በትጋት ለመለወጥ ትምህርት የሚወሰድበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበሰቃ ሃይቅ ላይ የተገነባውን ቤኑና መንደርን በዛሬው ዕለት መርቀው ከፍተዋል።
ቤኑና መንደር በበሰቃ ሃይቅ ዳርቻ እጅግ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎች፣ አዳራሽ፣ ሲኒማ ቤት የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ስፓ፣ እንዲሁም የፍራፍሬ ልማት እና የሌማት ትሩፋትን አካቶ የያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመንደሩ ግንባታም ባህላዊ የኪነ-ህንጻ ጥበብን ከዘመናዊ ግንባታ ጋር አቀናጅቶ የያዘ ሲሆን÷ ለአካባቢው ተጨማሪ የቱሪዝም አቅም የፈጠረ ወብ መዳረሻ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) መንደሩን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ቤኑና መንደር ይቻላልን በአይናችን ያየንበት ነው ብለዋል።
አካባቢው በጣም አስቸጋሪ የአየር ጸባይና መልክዓ ምድር እንዳለው ጠቅሰው÷ ይህን በመቋቋም ውብ ገጽታ ያለውን መንደር እውን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ይህም ፈተና ኢትዮጵያን ከመቀየር እንደማያቆመን ዳግም ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
መንደሩ ከመዝናኛ ስፍራዎች በተጨማሪ የፍራፍሬ ልማትና ሌማት ትሩፋትን ማካተቱ ደግሞ ግብርናን ከቱሪዝም መዳረሻ ጋር ለማስተሳሰር ትምህርት የሚወሰድበት ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በመንደሩ የብርቱካን ፣ ሎሚ፣ ፓፓዬ ማንጎ ልማት እንዲሁም ፣ ዶሮ፣ ግመል፣ ከብትና ፍየል የማርባት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የቤኑና መንደር ግንባታም በኢትዮጵያ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት ትብብር የተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
የስካይ ላይት ሆቴል መንደሩን ተረክቦ የማስተዳደር ስራ እንደሚያከናውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።