የቀድሞዋ የአሜሪካ ም/ቤት አፈ ጉባኤ ለዲሞክራቶች ሽንፈት ፕሬዚዳንት ባይደንን ተጠያቂ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞዋ የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ለዲሞክራቶች ሽንፈት ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ባይደን ከውድድሩ ቀደም ብለው እራሳቸውን አግልለው ቢሆን ኖሮ ዲሞክራቶች ሌሎች እጩዎች ሊኖራቸው ይችል ነበር ሲሉ በዋሽንግተን ተፅእኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ ናቸው የሚባሉት ፔሎሲ ተናግረዋል፡፡
ናንሲ ፔሎሲ ጆ ባይደን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የምርጫ ክርክር ያሳዩትን ደካማ አቋም ተከትሎ ከውድድሩ እራሳቸውን እንዲያገሉ ሲወተውቱና ጫና ሲያሳድሩ የነበሩ ግለሰብ ናቸው፡፡
ባይደን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተሰነዘረባቸው ጫና ከምርጫ ውድድሩ እራሳቸውን አግልለው ምክትላቸውን ካማላ ሃሪስን በእጩነት ቢያቀርቡም በሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ተሸንፈዋል፡፡
ጆ ባይደን ቀደም ብለው እራሳቸውን ከምርጫው ቢያገሉ ኖሮ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት በርካታ እጩዎችን ለማወዳደር እድል ይኖራቸው ነበር፤ ካማላ ሃሪስም በዚሁ ሂደት ውስጥ ያልፉ ነበር ብለዋል፡፡
አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የካማላ ሃሪስ ረዳትም ለዲሞክራቶች ሽንፈት ጣታቸውን በተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ላይ ቀስረዋል፡፡
ጥሩ የተባለ የይምረጡኝ ዘመቻ አካሂደናል፤ ለካማላ ሃሪስና ለዲሞክራቶች ሽንፋት ምክንያቱ ጆ ባይደን ናቸው ሲሉም መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዲሞክራቱና የፔንስሊቫኒያ ሴናተር ጆን ፌተርማን ግን በምርጫቸው ለመሸነፋቸው ጆ ባይደን ከምርጫ እራሳቸውን እንዲያገሉ ጫና ያሳደሩ ግለሰቦችን ወቅሰዋል፡፡