Fana: At a Speed of Life!

ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ  በአስተማማኝ ብቃት ላይ ይገኛል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ  በአስተማማኝ ብቃት ላይ ይገኛል ሲሉ የጦር ሀይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ፡፡

የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚና የሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የወልወል ድህረ-ምረቃ እና የ25ኛ ሰላም ኮርስ ዕጩ መኮንኖችን አስመርቋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ተመራቂዎች ለአመራርነት ብቁ የሚያደርጋቸውን ዕውቀት፣ ክህሎት እና ብቃት ጨብጠዋል።

ተመራቂዎች የመከላከያ ሠራዊቱን የመፈጸም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያሸጋግሩ ተስፋ የተጣለባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች እና የውስጥ ተላላኪ ኃይሎችን አፍራሽ ተግባር በታላቅ ብቃት እያከሸፈ ይገኛል ያሉት ፊልድ ማርሻሉ÷የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ  በአስተማማኝ ብቃት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የዛሬ ተመራቂዎችም የሠራዊቱን የድል አድራጊነት ጉዞ በታላቅ ሀገራዊ ስሜትና ጀግንነት ማስቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱ የዕድገት ጉዞ እንዲረጋገጥ ብሎም ሉዓላዊነቷ እንዲከበር በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ የጠላቶችን እና የቅጥረኞችን ሴራ በማሸነፍ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዕድገት ጉዞ ከግብ እንድታደርስ በሚያስችለው ብቃት ላይ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.