የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የ2017 በጀት ዓመት የልማታዊ ሴፍቲኔት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና የሥራ ፕሮጀክት ባለፉት አመታት የበርካታ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ያስቻለ አመርቂ ውጤት የተገኘበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ፕሮጀክቱ የከተማ ግብርና ሥራ የከተማ ነዋሪዎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተጨማሪ አቅም እየሆነ እንዲመጣ ማስቻሉ ተገልጿል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን÷ በበጀት አመቱ ከመንግስትና ከልማት አጋሮች በሚመደበው ተጨማሪ ሀብት በዘላቂ የቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ እና የምግብ ዋስትና ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ዓመታዊ በጀት 21 ቢሊየን ብር ሆኖ መፅደቁን አስታውሰው÷ በተጨማሪም መንግስት በቅርቡ ባካሄደው የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለ2017 የበጀት አመት 60 ቢሊየን ብር ለከተማና የገጠር ሴፍቲኔት ድጎማ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በአካባቢ ልማት ሥራዎች፣ በቀጥተኛ ድጋፍ፣ በልዩ ድጋፍ፣ በወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እንዲሁም ከስደት ተመላሾችን ጨምሮ በአጠቃላይ 1 ነጥብ 8 ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በቤዛዊት ከበደ