በሶማሌ ክልል በ300 ሚሊየን ብር ወጪ ማስፋፊያ የተደረገለት ሆስፒታል ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ በ300 ሚሊየን ብር ወጪ ማስፋፊያ የተደረገለት የጎዴ ከተማ ሼክ ኢብራሂም አብደላ አጠቃላይ ሆስፒታልና አዲስ የተገነባውን የኦክስጂን ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ።
አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በወቅቱ፤ ሆስፒታሉ ማሻሻያና የኦክሲጂን ማምረቻ ማዕከሉ ግንባታ መንግሥት ለጤና አገልግሎት መሻሻል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
የጤና አገልግሎት ጥራትን እንደሚያሳድግም ጨምረው ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ አዳዲስ የተኝቶ መታከሚያ ክፍሎች፣ የእናቶችና ህፃናት ማዕከል፣ የአስቸኳይና ልዩ ህክምና ክፍሎች፣ የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም የአገልግሎት መስጫ ማዕከልን ማካተቱ ተገልጿል።
በሆስፒታሉ የተደረገው የማስፋፊያ ሥራ የነበረውን የህሙማንና የታካሚዎች መጨናነቅ ይቀንሳል ተብሏል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሳ አህመድ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉና የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከሉ በጎዴ ከተማ ሥር የሚገኙ የጤና ማዕከላትን ጨምሮ በሸቤሌና አጎራባች ዞኖች የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጎላ ጠቀሜታን ያበረክታሉ።
የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከሉ በጅግጅጋ ከተማ ካለው ማዕከል ቀጥሎ በክልሉ ሁለተኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀን 150 ሲሊንደሮች የማምረት አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልል፣ የሸቤሌ ዞንና የጎዴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና የአጋር አካላት ተወካዮች መገኘታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ መረጃ አመልክቷል።